የሚሰሩ እጆችና የወጣቱን መንፈስ ይዘን የምግብ ዕርዳታ የምንጠይቅበት ሁኔታ ማብቃት አለበትጠ/ሚ መለስ

Posted on May 28, 2010

1


የሚሰሩ እጆችና የወጣቱን መንፈስ ይዘን የምግብ ዕርዳታ የምንጠይቅበት ሁኔታ ማብቃት አለበትጠ/ሚ መለስ
አዲስ አበባ, ግንቦት 20 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) – የሚሰሩ እጆች፣የሚያስብ አዕምሮና የወጣቱን መንፈስ ይዘን የምግብ ዕርዳታ የምንጠይቅበት ሁኔታ ማብቃት እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዛሬ 19ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል በሚሌኒየም አዳራሽ በተከበረበት ወቅት እንደተናገሩት የሚሰሩ እጆችና እንዲሁም የወጣቱን ተነሳሽነት ይዘን ምግብ ከመለመን መውጣት አለብን ብለዋል።

ለዛሬ ድል ያበቁንን ሰማዕታት ዋና ጠላት የሆነውን ድህነት ሳያገኙ የድህነት ዘበኛ የነበረውን የድርግ ሥርዓት ተፋልመው አልፈዋል ያሉት አቶ መለስ፣አሁን ግን የዋናው ጠላት ዘበኛ ባለመኖሩ ድህነትን ለመዋጋት ሕዝቡ ዝግጁ እንዲሆንም አስገንዝበዋል።

መንግሥት የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት ለማርካት ሌት ተቀን ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ እንደሚታገልም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አረጋግጠዋል ሲ ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ሰላምና ዴሞክራሲ የተጎናጸፉበት ቀን በመሆኗ ልዩ ክብር ይሰጣታል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተጀመረውን ልማት በተፋጠነ መልኩ ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸውን ጠብቀው አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት በአንድነት የሚቆሙባት መሆኗን አስታውቀዋል።

ሕዝቡ በአራተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢህአዴግ አመኔታ አሳድሮ ለመጪዎቹ ዓመታት አገሪቱን እንዲያስተዳድረው በመምረጡ አቶ ኩማ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በየአምስት ዓመቱ የሚመጣና የሚሄድ ሳይሆን፣የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሕይወት አካል ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

መንግሥት ወጣቱን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በበለጠ የልማቱ ተጠቃሚዎች ለማድረግ ጥረቱን እንደማያቋርጥም ገልጸዋል።

”ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሠረት”በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ በዓል ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት በድምቀት መከበሩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Advertisements
Posted in: Ethiopia