የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት የተወሰነውን ውሳኔ እንደሚደግፉት የሃረር፤ የአዳማ፤ የደሴና የጋምቤላ ነዋሪዎች አስታወቁ

Posted on December 12, 2006

0


የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት የተወሰነውን ውሳኔ እንደሚደግፉት የሃረር፤ የአዳማ፤ የደሴና የጋምቤላ ነዋሪዎች አስታወቁ

Posted: December 7th, 2006, 7:05pm EST
Tags
 
የተቃጣብንን ወረራ ለመመከት የተወሰነውን ውሳኔ እንደሚደግፉት የሃረር፤ የአዳማ፤ የደሴና የጋምቤላ ነዋሪዎች አስታወቁ
ሐረር ኀዳር 28/1999//ዋኢማ/በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የአዳማ፣የጋምቤላና የደሴ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ጥላ ስር የተሰባሰቡ አክራሪዎች በሀገራችን ላይ ያወጁትን ጦርነት ለመመከት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሚደግፉ አስታወቁ።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ሼክ ዳውድ ሙሳ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት ምክር ቤቱ የሶማሊያን ጉዳይ አስመልክቶ ያሳለፈው ውሳኔ ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል የተወሰደ ወቅታዊና ትክክለኛ እርምጃ በመሆኑ በዞኑ 18 ወረዳዎች የሚገኙ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች ደግፈውታል።

ውሳኔው ጂሀዲስቶቹ የኢትዮጵያ ሶማሌዎችን ብቻ ሳይሆን ከአዋሽ በታች ያሉ መሬቶችን በመቆጣጠር ታላቋን ሶማሊያ እንመሰርታለን የሚለውን የቀድሞዋ ሶማሊያ ተስፋፊ መሪዎችን ቅዥት በማንገብ ሀገራችንን ወደ ብጥብጥና ትርምስ ለመክተት ያሰቡትን ወራሪዎች ለመመመከት ያስችላል።

ሼክ ዳውድ እንዳሉት አክራሪዎቹ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን በእስልምና ሀይማኖት ሽፋን ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሚያናፍሱት አሉባልታ ከተቀደሰው የእስልምና ሀይማኖት ጋር የሚያዛምደው አንዳችም ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።

ይልቁምን አክራሪዎቹ የኤርትራን መንግስት ዓላማ ለማስፈጸም ከወራሪዎቹ ጎን ለተሰለፈው ኦነግና ለሌሎችም ፀረ ሰላም ሀይሎች ከለላ፣ መጠለያና ስልጠና በመስጠት ሀገራችንን በማፈራረስ ተግባር ላይ በጋራ መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ከመንግስትና ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ሀገሩን ከወራሪዎች ጥቃት የመከላከል ግዴታ እንዳለበት አስታውቀዋል።

በፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ያላቸው አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ያሳዩት መለሳለስ ና ልዩነት እንዳሳዘናቸው የገለጹት ሼክ ዳውድ ለሀገር ሉአላዊነት መስራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

በተመሳሳይም የጂዲስቶቹን የጦርነት አዋጅ አጥብቀው እንደሚቃወሙት በአዳማ ከተማ የሚገኙ የእስልምና ተከታዮች ገለፁ።

በከተማዋ 02 ቀበሌ የሚኖሩ ሀጂ ዲንቡ አብደላ እንዳሉት አክራሪ ሀይሉ ለብዙ ዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ በሃይማኖት ሽፋን ለመበታተንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚያደርገውን ግስጋሴ በእንጭጩ ሊገታ ይገባል ብለዋል።

አክራሪ ሃይሉ እየቃጣው ያለው አደጋ ከአይማኖት ነፃነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደለሌ ገልጸው ድርጊቱ ኢትዮጵያን ለመበታተንና ለማበጣበጥ የተሸረበ ሴራ በመሆኑ ሙሲሊሙ ሕብረተሰብ ከመንግስት ጎን መሰለፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አቶ አህመድ ሚደጋ በበኩላቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ የተላለፈው ውሳኔ ትክክልና ወቅታዊ ሆኖ እያለ አንዳንድ ተቃዋሚ ሀይሎቹ ውሳኔውን አለመቀበላቸው አክራሪውን ጥቃቱን እንዲቀጥል መፍቀድ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይም እስላማዊ አክራሪ ቡድኑ በሃይማኖት ሽፋን እያደረሰ ያለው ጥቃትን ለመከላከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉና ለተግባራዊነቱም የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በሰሜን ወሎና በዋግምራ ዞን ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አስታውቀዋል።

በመርሳና በሰቆጣ ከተሞች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትናንት በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት፤ የአክራሪ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያወጀው ጦርነት ሃይማኖትን ሽፋን የሚከናወን የአሸባሪነት ድርጊት መሆኑንና ጉዳዩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ሰላም በፅኑ የሚጎዳ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል።

በመሆኑም መንግስት የአክራሪ ቡድኑን ወረራ ለመመከት ያሳለፈው ውሳኔ የዘገየ ቢሆንም መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ፤ ለተግባራዊነቱ ግንባር ቀደም እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደርበው መንገሻና አቶ አዲሱ ሙሉጌታ እንደገለፁት ሃገርን ከውጭ ወራሪ ሃይል የመጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርሻ ሲሆን አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የተወሰነውን ውሳኔ መቃወማቸው አሳፋሪ ነው ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

Advertisements
Posted in: Uncategorized